አንድነት ፓርክ

ታሪካዊ

የአንድነት ፓርክ በጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የግንባታና የማደራጀት ሥራው በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ መስከረም 29፤ 2012 ዓ.ም ታላላቅ የሃገር መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት የተደረገ የቱሪስት መስህብ ነው፡፡

የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በውስጡም ልዩ ልዩ የታሪክ፣የተፈጥሮ እና የባሕል መስህቦችን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ የአንድነት ፓርክ የሚገኝበት ታላቁ ቤተ መንግሥት የተቆረቆረው በ1878 ዓ.ም. ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሳይጨምር የሰባት መሪዎች የሥራና የመኖሪያ ቦታ በመሆን አገልግሏል፡፡ ቤተ መንግሥቱ 40 ሄክታር ሥፋት ያለው ሲሆን ከዳግማዊ ዐጼ ምኒሊክ ዘመን ጀምሮ የተገነቡ ልዩ ልዩ ሕንጻዎችንና በእጽዋት የተሞላ ሰፊ ሥፍራን ይዟል፡፡

የግብር አዳራሽ የተገነባው በዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ዘመን በ1890-91 ዓ.ም. ነው፡፡ አዳራሹ በተሠራበት ዘመን ንጉሠ ነገሥቱ ዘወትር ግብር ያበሉበት የነበረ ሲሆን በሂደት ግን ሕዝቡ እየበረከተ ስለሄደ ግብር የማብላቱ ሥርዓት በታላላቅ ሃይማኖታዊ እና በዘውድ በዓላት ብቻ ተወስኗል፡፡ የግብር አዳራሹ በተለያዩ ዘመናት ታላላቅ ታሪካዊ ሁነቶችን አስተናግዷል፡፡ በ1955 ዓ.ም. ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ በአዲስ አበባ የተገኙ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች መንግሥታዊ እራት ተጋብዘውበታል፡፡ በ1972 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) ጉባዔ ተካሂዶበታል፡፡ በቅርቡም በግንቦት 2011 ዓ.ም. በገበታ ለሸገር ዝግጅት አማካኝነት አዲስ አበባን ለማስዋብ 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የእራት መስተንግዶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተካሂዶበታል፡፡ የግብር አዳራሹ በየዘመኑ እድሳት ሲደረግለት ቆይቷል፡፡

ህንጻ

ዙፋን ቤት

ዙፋን ቤት አንድ መቶ ዓመታት ገደማ እድሜ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ሕንጻ ላይኛው አዳራሽ የነገሥታቱ ዙፋን የሚቀመጥበት ሆኖ መሪዎቹ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚመጡ እንግዶቻቸውን የሚቀበሉበት፣የሚመክሩበትና በጀርባውም ባለው ክፍል ግብዣ የሚያደርጉበት ነበር፡፡ ምድር ቤቱ በዘመኑ ለመጠጥ ማስቀመጫነት (ማቀዝቀዣነት) አገልግሎት ይውል ነበር፡፡ የዙፋን ቤቱ ላይኛው ክፍል ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የደርግ አባላት መሠብሰቢያ አዳረሽ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ምድር ቤቱ ደግሞ የንጉሠ ነገሥቱ ባለሥልጣናት ለሥምንት ዓመታት የታሠሩበትና በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የተለያዩ እስረኞች የተሠቃዩበትና የተገደሉበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአንድነት ፓርክ ሙዝየም ዋና ዐውደ ርዕይ በዚህ ሕንጻ ውስጥ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፤ እምነቶች እንዲሁም የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተገነባች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሙዝየሙ ዐውደ ርዕዮች እነዚህን የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ባህላዊ ዕሴቶች በጥቂቱ የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ዙፋኑ የሚገኝበትን ክፍል ጨምሮ በግራ፣ በቀኝ፣ በጀርባና ምድር ቤት ውስጥ ሕንጻው አምስት የዐውደ ርዕይ ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የዙፋን ክፍል፣ የእምነት፣ የአፈታሪክ፣ የመንግስታት እና የአቢዮቱና የቀይ ሽብር ዐውደ ርዕዮች ናቸው፡፡

የዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ቤተ-መንግስት እልፍኞች ግንባታ የተጀመረው በ1880ዎቹ አጋማሽ ነው፡፡ ስብስቡ በተለምዶ እንቁላል ቤት ተብሎ የሚታወቀውን ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ ጨምሮ በመተላለፊያ ሠገነት ተያይዘው የተሠሩት ቤቶች የዐጼ ምኒልክ መኝታ ቤትና እልፍኝ፣ የእቴጌ ጣይቱ መኝታ ቤትና እልፍኝ፣ የእልፍኝ አዳራሽን እና የልዑላን መኝታ ቤቶችን ያጠቃልላል፡፡ በጣራው ቅርጽ ምክንያት እንቁላል ቤት ተብሎ የሚታወቀው ባለሁለት ፎቅ ሕንጻ የዳግማዊ ምኒልክ ጸሎት ቤት፣የቅኝት ሠገነት እና ጽ/ቤት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ እንዲሁም በጸሎት ቤቱ መግቢያ አካባቢ ላይ የተገጠመው የድምጽ ማስተላለፊያ ቱቦ ጸሎት ቤቱን ከጽሕፈት ቤቱ ጋር የሚያገናኝ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሰልክ የተቀመጠባቸው ሁለት ትንንሽ ክፍሎች ወደ ዐፄ ምኒልክ መኝታ ቤት በሚወስደው መተላለፊያ ኮሪደር ውስጥ በስተግራና በቀኝ ይገኛሉ፡፡ በወደ ምስራቅ አቅጣጫ ተነጥሎ የሚታየው እና የእንጨት ግድግዳ ያለው ቤት በ1923 ዓ.ም. የተገነባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሠብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን፤ በወደ ምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ የዳግማዊ ምኒሊክ እልፍኝ አቅራቢያ የሚገኘው ባለአንድ ክፍል አነስተኛ ቤት የጦር ሚኒስትሩ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) መቆያ ክፍል ነው፡፡

የክልሎች እልፍኞች የተገነቡት በ2011 ዓ.ም. ሲሆን የየክልሎቹን ባህል፣ታሪክ፣ ቅርስ፣ የተፈጥሮ ሀብትና የመዋዕለ ንዋይ መስህብ የሚገለጹ መረጃዎችን ይዘዋል፡፡ በዘመናዊ የጥበብ ሥልት የተደራጁት የክልሎች እልፍኞች ጎብኚዎች ስለ አገራችን ሕዝቦች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ምቹና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በምስልና ድምፅ፣ በስዕላዊ ገለፃ እና በተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች ግንዛቤ እንዲጨብጡበት ተደርገው የተደራጁ ናቸው፡፡

የሃገር በቀል እፅዋት ማሳያ በውስጡ የተለያዩ አገር በቀል እፅዋትን እና የግንባታ ዘዴዎችን ለጎብኚዎች የሚያሳይ የጉብኝት ማዕከል ነው። በዚህ ስፍራ ውስጥ በዋነኝነት ለመድሃኒትነት፣ ለውበት፣ ለቅመማ ቅመምነት፣ ለምግብና መጠጥ ዝግጅት፣ ለእንጨት ስራ እና ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ሃገር በቀል እፅዋት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የገጠሩን አኗኗር፣ የቤት አሠራር ጥበብና ስነ-ምድራዊ ገፅታ ማራኪ በሆነ መንገድ ለጎብኚዎች ያቀርባል፡፡ በሌላ መልኩ በዚህ ስፍራ በሁለት ግመሎች እና በኤሊ ቅርፅ የተሰሩ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ የግመል ቤቶቹ ለህፃናት የተለያዩ ትምህርት ሰጪ የሆኑ ቪዲዮዎች የሚታዩባቸው እና የስነ-ጥበብ ስራዎችን መለማመጃ ክፍሎችን በውስጣቸው የያዙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግቢው ውስጥ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ እና አርጅተው ከወደቁ ዛፎች የተሰሩ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች የስፍራው ድምቀቶች ናቸው፡፡ የሃገር በቀል እፅዋት ማሳያ ስፍራን ከሌሎች መስህቦች ለየት የሚያደርገው ሙሉ በሙሉ በሰው እጅ ያለ ማሽን እገዛ የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተሰበሰቡ የእፅዋት፣ የካብ፣ የድንጋይ ስራ፣ የባህላዊ ቤት ግንባታ እና ሌሎች ሙያተኞች የተሳተፉበት ነው፡፡

የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት በአንድነት ፓርክ ከሚገኙ ሁለት መካነ-እንስሳት ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ ይህ ስፍራ የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት ተብሎ የተሰየመው በሃገራችን ብቻ ከሚገኘው ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በመነሳት ነው፡፡ ይህ ባለጥቁር ጎፈር አንበሳ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ዴዴሳ እና አልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ በዋነኛነት የሚገኝ ነው፡፡ መካነ-እንስሳቱ የጥቁር አናብስት እና የሰጎኖች ዐውደ ርዕዮችን አቅፎ ይገኛል፡፡ በዚህ መካነ-እንስሳት ርዝመቱ 175 ሜትር የሚሆን ሰው ሰራሽ ዋሻ ሚገኝ ሲሆን፤ ጎብኚዎች ውስጥ ለውስጥ በዋሻው በመንቀሳቀስ ለእይታ ተብለው በተዘጋጁ ሰፋፊ የመስታወት መስኮቶች ውስጥ የእንስሳቱን እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ፡፡ በሌላ በኩል እንስሳቱ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሆኖ በተዘጋጀላቸው ሰፊ ስፍራ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ በተጨማሪም ይህ ስፍራ ለእንስሳቱ ማደሪያ፤ ምግብ ማቀነባበሪያ እና ህክምና መስጫ፤ እና የጎብኚዎች ማረፊያ ካፍቴሪያን በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡

ተፈጥሮ

የአንድነት መካነ-እንስሳት

የአንድነት መካነ-እንስሳት 37 አጥቢ እንስሳት እና የአእዋፍ ዝርያዎችን በውስጡ አቅፎ የሚገኝ በአይነቱ በሃገራችን የመጀመሪያው መካነ-እንስሳት ነው፡፡ በመካነ-እንስሳቱ ዘጠኝ የዐውደ ርዕይ ስፍራዎች የሚገኙ ሲሆን እነሱም የሚርካት፣ የውሃ ውስጥ እንስሳት ማሳያ (አኳሪየም)፣ የፒኮክ፣ የአቦ ሸማኔ፣ የነጭ አንበሳ፣ የተኩላ፣ የጭላዳ ዝንጀሮ፣ የአዕዋፍ እና ሳፋሪ ዐውደ ርዕዮች ናቸው፡፡ በሃገራችን የመጀመሪያ የሆነው የውሃ ውስጥ እንስሳት ማሳያ (አኳሪየም) በአንድነት መካነ-እንስሳት የሚገኝ ሲሆን ከአስራ ሶስት በላይ የአሳ ዝርያዎችን በሶስት አይነት ኤግዚቢሽኖች ለጎብኚዎች የሚታዩበት ስፍራ ነው፡፡ ሌላው በመካነ-እንስሳቱ ውስጥ ለየት ባለ ሁኔታ የተዘጋጀው የሰው ሰራሽ የወፍ ጎጆ (Aviary) ሲሆን፤ ከትናንሽ እስከ ግዙፍ የአዕዋፍ ዝርያዎችን በጣም ማራኪ በሆነ ሁኔታ ለጎብኚዎች እንዲታይ የተዘጋጀ ነው፡፡ የዚህ መካነ-እንስሳት ሌላኛው ድምቀት የሳፋሪ አውደ ርዕይ ሲሆን በውስጡም ዘጠኝ አይነት እንስሳት የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ቶራ ፈረስ፣ የደጋ አጋዘን፣ ኢምፓላ፣ ውድንቢ፣ ሳላ፣ የቆላ አጋዘን እና ነጭ አውራሪስ ናቸው፡፡ በፓርካችን የተቋቋሙት ሁለት መካነ-እንስሳት ማለትም የጥቁር አንበሳ መካነ-እንስሳት እና የአንድነት መካነ እንስሳት የዱር እንስሳቱን ተፈጥሯዊ አካባቢቢ በሚመስል መንገድ ተፈጥሯዊ ገፅታን ተላብሰው የተገነቡ ናቸው፡፡